በሰላም የመለያየት ሕግ
“የሰውን አእምሮ የሚያዞሩ ሁለት አስቸጋሪ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከእኛ ጋር አብሮ መቆየት የማይፈልግን ሰው እንዴት እንዲቆይ ማድረግ ይቻላል? ከእኛ ተለይቶ ለመሄድ የማይፈልግን ሰውስ እንዴት እንዲሄድ ማድረግ ይቻላል? - Danny Devito
ከሰዎች ጋር ሰላም የመሆንን ትርጉም የግድ ከሰዎቹ ጋር አብሮ ከመዋልና ከማደር ጋር አዛምደው የሚያዩ ሰዎች አሉ፡፡ ይህ አይነቱ አመለካከት ከባህላዊ እይታ ጋር የሚዛመድ ጉዳይ ነው፡፡ በማሕበራዊ ትስስር የጠነከረ ሕብረተሰብ ውስጥ ስምንኖር፣ መለያየት የሚባለው ሃሳብ በስሜታችን ውስጥ ጠሊቅ ስፍራ አለው፡፡
መለያየት በራሱ ክፉ ወይም መልካም አይደለም፡፡ ከአንድ ሰው ጋር የተለያየንበት ምክንያትና የመለያየቱን ሂደት ተግባራዊ ስናደርግ የወሰድናቸው እርምጃዎች ያንን ተግባር ክፉ ወይም መልካም ያደርጉታል፡፡ ያም ሆነ ይህ፣ አንዳንድ ጊዜ ከሰዎች ጋር የምንለያይባቸው ሁኔታዎች ሊከሰቱ በሰላም መለያየት አስፈላጊ የሚሆኑበት ጊዜ አለ፡፡
ከግለሰብም ሆነ ከማሕበራዊ ግንኙነቶች አንጻር በሆነ ባልሆነው ምክንያት መለየትን ያለመብሰል ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም፣ አንድን ግንኙነት የማቋረጥንና ከሰዎች የመለየትን ሁኔታ ስናስብ ያንን ውሳኔያችንን የሚነኩ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች እንዳሉ ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡፡
የግንኙነታችን ጥልቀትና ትስስር
ቀደም ብለን እንደጠቀስነው ከአንድ ሰው ጋር ያለን አለመግባባት ስለበዛ ብቻ ለመለያየት መወሰን አንችልም፡፡ ከሰዎቹ ጋር የግንኙነት ሁኔታና ጥልቀት ወደ ስሌቱ ሊገባ ያስፈልጋል፡፡ የትዳር ኪዳን ያለበት ትስስር፣ የዝምድና ሁኔታ፣ ከተለያየን በኋላ ተከታይ ሁኔታዎችን ያቀፈ ግንኙነትና መሰል የግንኙነት ዘርፎች በሚገባ ልናስብባቸው ይገባል፡፡
መለያየትን የጋበዘው ሁኔታ
ከሰዎች ጋር ያለንን አለመስማማት ለማስተካከል የተቻለንን ያህል ከሞከርን በኋላ በሰላም የመለያየትን ሕግ ተግባራዊ ከማድረጋችን በፊት ሌላ ልናስብበት የሚገባን ጉዳይ የችግሩ መደጋገምና ድርጊቱን የሚፈጽመው ሰው የመነሻ ሃሳብ ነው፡፡ ሰዎች ጤና-ቢስ በሆነ የመነሻ ሃሳብ ወደ አለመስማማት የሚወስዱ ችግሮችን ደጋግመው ሲፈጥሩ ከእነሱ ለመለየት የሚኖረንን ውሳኔ አንድ እርምጃ እንድንወስደው ማድረጉ ትክክለኛ ሁኔታ ነው፡፡
ባለመለያየት ውስጥ ሊከተል የሚችለው መዘዝ
አንዳንድ ከሰዎች ጋር የሚኖሩንን አለመግባባቶች በየወቅቱ ጊዜያዊም ሆነ ቋሚ መፍትሄዎችን እየፈለግንላቸው ስንቆይ ሊከተለው የሚችለው ችግር የከረረ ከሆነ በሰላም የመለየትን ሁኔታ በሚገባ ልናስብበት ይገባል፡፡ ሊፈጠር የሚችለው ችግር ግን አናሳ ከሆነ ከሰዎች የመለየትን ጉዳይ ልንቸኩልበት አይገባም፡፡
የሚዛናዊነት ሃሳቦች፡-
1. አንዳንድ ጊዜ ከሰዎች በሰላም የመለየትን ሁኔታ ማስቀረት የማንችልበት ጊዜ እንዳለ አምነን መቀል አለብን፡፡
2. መለያየት ማለት የግድ መከፋፋት ማለት እንዳልሆነ በመገንዘብ ከሰዎች ከተለየን በኋላ ጤናማና ቅን አመለካከትን ይዘን መቆየቱ የሚጠቅመው ለእኛው መሆኑን ማስታወስ መልካም ነው፡፡
3. ጸብ፣ ክፋትና ቂም-በቀል ያለበት አብሮነትም ሆነ መለያየት ጤና ቢስ መሆኑን ተገንዝበን ውሳኔያችን ምንም ሆነ ምን ከእነዚህ መርዛማ ዝንባሌዎች ራሳችንን መጠበቅ መልካም ነው፡፡
4. ወዳጅነት ማለት የግድ አብሮ መኖርና አብሮ ውሎ ማደር ማለት እንዳልሆነ ማስተወስ አለብን፡፡ ብዙ የማይገናኙ ጥብቅ ወዳጆች የመኖራቸውን ያህል፣ ብዙ ትስስርና ግንኙነት እያላቸው ጠላትነትን በውስጣቸው ይዘው የሚኖሩም ሰዎች አንዳሉ ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡፡
5. ከሰዎቹ ጋር ያለን የግንኙነት ጥልቀትና ደረጃ የመለያየቱን ሁኔታ በሚገባ አስበንበት እንድናደርገው የማስገደዱ ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሁል ጊዜ በተቻለ መጠን ከመለያየት ይልቅ አብሮነት የሚመረጥ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡
6. ከሰዎች ጋር አብሮ መሆን የሚመረጥና ሁል ጊዜ ልንጠብቀው የሚገባን ሁኔታ ቢሆንም፣ አብረን መቀጠል ከማንችላቸው ሰዎች ውጪ ሙሉ ሰዎች ሆነን መኖር እንደምንችልም ማስታወስ ስሜታችንን ከውድቀት ይጠብቀዋል፡፡
በቅንነት ሼር ያድርጉልኝ 👇
http://t.me/psychologypages