ደዕዋ ላይ ለተሰማራችሁ ሁሉ!
~
የአላህ መልእክተኛ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦
" مَنْ رَأَى مِنْكُمْ مُنْكَرًا فَلْيُغَيِّرْهُ بِيَدِهِ، فَإِنْ لَمْ يَسْتَطِعْ فَبِلِسَانِهِ، فَإِنْ لَمْ يَسْتَطِعْ فَبِقَلْبِهِ، وَذَلِكَ أَضْعَفُ الْإِيمَانِ "
"ከናንተ መጥፎን ነገር ያየ በእጁ ይቀይረው። ካልቻለ በምላሱ፤ ካልቻለ ደግሞ በልቡ። ይሄኛው የመጨረሻ ደካማው እምነት ነው።" [ሙስሊም: 186]
ስለዚህ ያዩትን መጥፎ ነገር ማስወገድ ኢስላማዊ ኃላፊነት ነው። ቀጥታ ማስወገድ ካልተቻለ በቃል ወይም በፅሁፍ መናገር ይገባል። ይሄ ጉዳይ የሁሉም ሙስሊም ግዴታ ቢሆንም የዱዓት ኃላፊነት ግን ከሌሎች የከበደ ነው። ስለዚህ በሃገር በአካባቢያችሁ የሚታዩ ችግሮች ላይ እርምት መስጠት ይገባል። ሁሉም በዝምታ ከተሰማማ ጥፋቱ 'ኖርማል' እየተደረገ ይያዛል።
ባይሆን ሁለት ነገሮችን ማስተዋል ጥሩ ነው።
1ኛ፦ ባደባባይ የሚፈፀሙ ጥፋቶችን ወይም አሳሳች ስብከቶችን ማረም የነፍስ ወከፍ ሳይሆን የጋራ ግዴታ ነው፣ ፈርዶል ኪፋያ። ስለዚህ ከፊሎች ይህንን ኃላፊነት ከተወጡ ሌሎች ከተጠያቂነት ይድናሉ። ስለዚህ በንዲህ አይነት ሁኔታ ያልተናገረውን ሁሉ ወንጀለኛ ማድረግ አይቻልም።
2ኛ፦ ያያችሁትን ጥፋት ስታስጠነቅቁ በራሳችሁም ይሁን በደዕዋችሁ ላይ የባሰ ጥፋት የሚከተል ከሆነ በመጀመሪያ ግራ ቀኝ ማየት ይገባል። አጥፊዎች ጉልበት ያላቸውና የተደራጁ በመሆናቸው የተነሳ አንድ ጥፋት ላይ ስትናገሩ ደዕዋችሁን በእጅጉ በሚጎዳ መልኩ የሚያሰናክሏችሁ ከሆነ ለተሻለው ጥቅም ስትሉ ለጊዜው ዝቅ ብላችሁ አሳልፉት።
ብትናገሩ ምን ሊከተል እንደሚችል እየገመታችሁ ሳለ ነገር ግን በቡድናዊ ልዩነት ተነሳስቶ ወይም በእልህ ተገፋፍቶ "ዛሬውኑ ካልጮሃችሁ" ብሎ ለሚጫናችሁ አካል እጅ ሰጥታችሁ ብትናገሩ ይሄ ኢኽላስ ሳይሆን ይዩልኝ፣ ይስሙልኝ ነው የሚሆነው። ይሄ ደግሞ ሺርክ እንደሆነ እንዳትረሱ! በዚህ መልኩ በመናገራችሁ መስጂዳችሁን ብትነጠቁ ወይም ደዕዋችሁ ቢሰናከል ድርብርብ ወንጀለኛ ትሆናላችሁ። እጅ ጠምዝዘው ያለ ጊዜው እንድትናገሩ ሊያስገድዷችሁ የሚሞክሩ አካላትንም አታስደስቱም። ስለዚህ ከመነሻው በሚገባ መዝናችሁ ተናገሩ። ባይሆን በቦታው መናገር ሲጠበቅባችሁ ጊዜ ፍርሃታችሁን በ 'መስለሓ' ስም እየሸፈናችሁ ራሳችሁን እንዳትሸውዱ። አስተውሉ! ፍርሃት ለራስ ሲሆን ጥንቃቄ ነው ስሙ፡፡ የፈሪዎች ሂሳብ!
አንድ ነገር ግን እንዳይዘነጋ። 'መስለሓ' እና 'መፍሰዳ'ን በመገመት ላይ የሰዎች እይታ የሚለያይበት ብዙ አጋጣሚ አለ። በዚህን ጊዜ ሰዎችን ልባቸውን ለአላህ በመተው የታያቸውን ነገር በኢኽላስ እንዲያደርጉ መተው ይገባል። በመሰል ሁኔታዎች ላይ መናገሩ የተሻለ ሆኖ የታየው አካል ይናገር። በመናገሩ የከፋ ነገር ይከተላል የሚል ስጋት ያለው ዝም ይበል። በ'ንዲህ አይነት ሁኔታ ላይ አንዱ ሌላውን በራሱ ሃሳብ ሊያስገድድም ሊወነጅልም አይችልም። ያለበለዚያ የሚቀረው ምርጫ መናቆርና መለያየት ብቻ ነው። ከዚያ መሬት ላይ ከሚታየው ጥፋት ይልቅ በጎንዮሽ ልፊያ መጠመድ ይከተላል።
ብልጥ ማለት አላህ ማስተዋልን ያደለው ነው። አስፈላጊ ሲሆን የወቃሽን ወቀሳ ሳይፈራ ጀግና የሚሆን፣ የጥፋት ኃይሎችን እስከ ጥግ በድፍረት የሚጋፈጥ። መጋፈጡ የባሰ ጣጣ እንደሚያስከትል ሲያምን ደግሞ ስሜቱን የሚቆጣጠር፤ ራሱን የሚያሸንፍ፤ የራሱን ሃሳብ ሌሎች ላይ ካልጫንኩ ብሎ ሁከት የማይፈጥር። አላህ ማስተዋሉን ያድለን።
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://t.me/IbnuMunewor